የሪል እስቴት ግንባታው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይጀመራል
ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ከሚሰማራባቸው አዳዲስ የንግድ ዘርፎች አንዱ የሆነው የሪል እስቴት ግንባታ ዘርፍ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ተገለፀ፡፡
አክሲዮን ማህበሩ 8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውንና 7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በግሎባል ሆቴል ባካሄደበት ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አሰፋ የ2012 ዓ.ም አመታዊ ሪፖርትን ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል፡፡ በሪፖርቱ እንደተመላከተው ድርጅቱ የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከርና የባለአክሲዮኖችን ፍላጎት ለማሳካት ታስቦ ለሪል እስቴት ግንባታው ዘርፍ የሚሆን የቦታ ግዥ መፈፀሙንና የአፓርትመንቱን ዲዛይን ከሚሰራ ድርጅት ጋር ውል ስለመፈፀሙ በባለፈው አመት ጠቅላላ ጉባዔ መገለፁን ያስታወሱት የቦርድ ሰብሳቢው ግንባታውን ለማከናወን የሾሪንግ ኮንትራክተር መረጣ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የዋና ኮንትራክተር እና አማካሪ ድርጅት መረጣ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም የገለፁት አቶ ታደሰ፤ ለግንባታው የሚያስፈልገው ገንዘብ ከባንክ በብድር በመገኘቱ ግንባታውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመጀመር ውጥን መያዙን በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሃያ ሁለት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባው ህንፃ ሶስት ቤዝመንቶች፣ አንድ ግራውንድ እና 15 ወለሎች ይኖሩታል።
በድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ ፌስቡክ https://www.facebook.com/Esdros-Construction-Trade-and-Industry-SC-282021025628947 ይከታተሉ።