በባህርዳር ቅርንጫፍ ውይይት ተካሄደ
የኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድ እና ኢንዱስትሪ አ.ማ የቦርድ ሰብሳቢ እና አባላት እንዲሁም የዋናው መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች በባህርዳር አቡነ ጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ት/ቤት በመገኘት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ፡፡
ውይይቱ ከተደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከማኅበረ ቅዱሳን ባህርዳር ማዕከል ጋር በጅምር በቆዩ ስራዎች እና ወደፊትም አብሮ ከመስራት አንጻር የተደረገ ስብሰባ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን ባህርዳር ማዕከል ሰብሳቢ፣ምክትል ሰብሳቢ እና ሥራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት ውይይቱ ተከናውኗል፡፡
በዕለቱ በሶስት ርዕሰ ጉዳዮች የትምህርት ቤት የኪራይ ውል፣ ከመኪና ጋር በተያያዘ ጥያቄ እና በባህርዳር ቅርንጫፍ ትምህርት አሰጣጥ እና ጥራት ዙሪያ ላይ በማተኮር ውይይት ተደርጓል፡፡
በመቀጠል የባህርዳር ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እና ርዕሰ መምህራን፣ የባህርዳር የሦስቱም ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቶች ወላጅ ተማሪ መምህራን ህብረት(ወተመህ) ሰብሳቢዎች እና አባላት በተገኙበት ወቅታዊ ሁኔታን መሰረት ያደረገ ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን በዋናነት ሥልጣንን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር በባህርዳር ቅርንጫፍ ክፍተት እንደነበር የጋራ ግንዛቤ በመውሰድ መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም ከባህርዳር ቅርንጫፍ የስራ ኃላፊዎች እና ርዕሰ መምህራን ጋር በተደረገ ውይይት አስተዳደራዊ ችግሮች እና ለመማር ማስተማር ሂደቱ ጠቃሚ የሆኑ ግብአቶች እንዲሟሉ ጥቄዎች በመነሳት የመፍትሄ ሀሳቦች ተቀምጠዋል፡፡
በመሆኑም የቅርንጫፉ የስራ ኃላፊዎች እና ርዕሰ መምህራኑ በየሳምንቱ በመሰብሰብ ተግባራታቸውን እንዲገመግሙና የውይይታቸውን ቃለ-ጉባኤ ችግሮቹ እስኪፈቱ ለዋና መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች እና ለቦርድ እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ እንዲሁም በተዋረድ የአፈጻጸም ግምገማ እንዲሰሩ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን የግዢ መጓተትን ለመቅረፍ የመፈጸሚያ ጊዜ በየደረጃው እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
በአጠቃላይ በቅርንጫፉ የተደረገው ውይይት ውጤታማ የነበረ፣ ችግሮችን ማየት ያስቻለ እና ለችግሮቹ የመፍትሄ ሃሳቦችን ቦርዱ በማስቀመጥ አቅጣጫዎችን የጠቆመበት ነው፡፡