አክሲዮን ማህበሩ የታክስ ህግ ተገዥነት ተሸላሚ ሆነ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ በ2012 በጀት አመት ለታክስ ህግ ተገዥነት ባስመዘገበው ውጤት በገቢዎች ሚኒስቴር ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የመካከለኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግ ተገዥነትን በማክበርና በመተግበር የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የንግድ ተቋማት የኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር ህዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም ባዘጋጀው የሽልማትና እውቅና ፕሮግራም ላይ ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ለታክስ ህጉ ተገዥ በመሆን ላስመዘገበው ውጤት የዋንጫና ምስክር ወረቀት ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

በካፒታል ሆቴል በተካሄደው በዚህ ስነስርዓት ላይ አክሲዮን ማህበሩ በቀጣይም ለህግ ተገዥነትን የንግድ እንቅስቃሴው መርህ አድርጎ ግብሩን በወቅቱና በአግባቡ እንደሚከፍል በአዘጋጆቹ እምነት እንደተጣለበት የተገለፀ ሲሆን ሽልማቱን የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ተቀብለዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ ትውልድን በማነፅ ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋን በማፍራት ላይ የሚገኘው ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ሁሉንም የግብር አይነቶች በታክስ ህጉ መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እየከፈለ ሲሆን ይህም ማህበሩ ከተቋቋመለት አላማ አንፃር የሚጠበቅ እና በትኩረት የሚሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አክሲዮን ማህበሩ በየአመቱ ሂሳቡን ኦዲት በማስደረግ ለገቢዎች እያሳወቀ ሲሆን ታክሱን በተገቢው ጊዜና መጠን እየከፈለ እንደሚገኝ በዚህም ለሽልማት መብቃቱን አቶ ተስፋየ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ሽልማቱ ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ በተሰማራባቸውና ወደፊትም ሊሰራቸው በእንቅስቃሴ ላይ በሚገኝባቸው የስራ ዘርፎች ግብሩን በታማኝነት በመክፈልና ለታክስ ህጉ ተገዥ በመሆን የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስቻለው መሆኑን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡