የአቡነ ጎርጎርዮስ ተማሪዎች የጻፏቸውን መጻሕፍት አስመረቁ

የአቡነ ጎርጎርዮስ አዋሬ ሁለተኛ ደረጃ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤት ተማሪ በሆኑት ቅዱስ የሺዋስ እና ህሊና የሺዋስ የተጻፉ ሦስት መጻሕፍት ህፃናትን ጨምሮ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተመርቀው ለአንባቢያን ቀረቡ፡፡
የአውሮፕላን የበረራ ምስጢሮች ጸሀፊ የሆነው ተማሪ ቅዱስ የሺዋስ ‘The Fundamentals of Airplane design’ በሚል ርዕስ ሁለተኛ ሥራውን ለአንባቢያን ያቀረበ ሲሆን እህቱ ህሊና የሺዋስ ደግሞ ስለ ልብ የተነገሩ ምርጥ አባባሎች እና ‘Anatomy & Physiology of the Heart’ የተሰኙ ሁለት መጻሕፍትን ለአንባቢያን አቅርባለች።
ተማሪዎቹ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ስለ ጻፉት መጽሐፍ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ተማሪ ህሊና ‘Anatomy & Physiology of the Heart’ በሚል ርእስ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የጻፈችው መጽሐፍ 12 ምዕራፎች እንዳሉት እና የመጽሐፉ ዋናው ክፍል ምዕራፍ 5 ስለ አራቱ የልብ ክፍሎች የሚተነትነው ርዕስ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
እንዲሁም ስለ ልብ የተነገሩ ምርጥ አባባሎች በሚል ርዕስ ያሳተመችው ሌላው መጽሐፍ በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በአረብኛ እና በግዕዝ ቋንቋዎች የተጻፈ ነው፡፡ መጽሐፉ የአባባሎች ስብስብ እንደሆነ የገለጸችው ጸሀፊዋ ከተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ድረ ገጾች እና መጽሐፍትን በማንበብ ያሰባሰበቻቸው ምሳሌያዊ አነጋገሮች የተካተቱበት እንደሆነ ተናግራች፡፡
ተማሪ ቅዱስ የሺዋስ ‘The Fundamentals of Airplane design’ በሚል ርዕስ የጻፈው መጽሐፍ 5 ምእራፎች እንዳሉት በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የገለጸ ሲሆን በዋናት መጽሐፉ አውሮፕላን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተፈጠረ ጀምሮ እንዴት በዲዛይን እየተሻሻለ እንደመጣ የሚያብራራ ነው ብሏል፡፡
ተማሪ ህሊና የልብ ሐኪም በመሆን በልብ በሽታ የተያዙ ህጻናትን መርዳት ህልሟ እንደሆነ ስትናገር ተማሪ ቅዱስ የሺዋስ ደግሞ የራሱ የሆነ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል የአውሮፕላን ዲዛይን የመስራት አላማ እንዳለው ተናግሯል፡፡