Abune gorgorios

እንኳን ደስ ያላችሁ

በአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች የለቡ ቅርንጫፍ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ክላስተር ማዕከል ስር ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ጋር በተደረገ የጥያቄና መልስ ውድድር የሚከተለውን ውጤት ማስመዝገብና ተሸላሚ መሆን ችሏል፡

1. በክላስተር ማዕከሉ ካሉ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ጋር በተደረገ የ8ኛ ክፍል ውድድር 2ኛ መውጣት ችሏል፡፡

2. በክላስተር ማዕከሉ ካሉ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ጋር በተደረገ የ4ኛ ክፍል ውድድር ከ3 ትምህርት ቤቶች ጋር እኩል ውጤት በማምጣት በተደረገ የመለያ ውድድር 3ኛ መውጣት ችሏል፡፡

 

የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/a/ እና የቴሌግራም ቻናል https://t.me/Esdrossc ይከታተሉ፡፡

የሪል እስቴት ግንባታው ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይጀመራል

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ከሚሰማራባቸው አዳዲስ የንግድ ዘርፎች አንዱ የሆነው የሪል እስቴት ግንባታ ዘርፍ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ተገለፀ፡፡

አክሲዮን ማህበሩ 8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውንና 7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በግሎባል ሆቴል ባካሄደበት ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አሰፋ የ2012 ዓ.ም አመታዊ ሪፖርትን ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል፡፡ በሪፖርቱ እንደተመላከተው ድርጅቱ የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከርና የባለአክሲዮኖችን ፍላጎት ለማሳካት ታስቦ ለሪል እስቴት ግንባታው ዘርፍ የሚሆን የቦታ ግዥ መፈፀሙንና የአፓርትመንቱን ዲዛይን ከሚሰራ ድርጅት ጋር ውል ስለመፈፀሙ በባለፈው አመት ጠቅላላ ጉባዔ መገለፁን ያስታወሱት የቦርድ ሰብሳቢው ግንባታውን ለማከናወን የሾሪንግ ኮንትራክተር መረጣ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

የዋና ኮንትራክተር እና አማካሪ ድርጅት መረጣ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም የገለፁት አቶ ታደሰ፤ ለግንባታው የሚያስፈልገው ገንዘብ ከባንክ በብድር በመገኘቱ ግንባታውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለመጀመር ውጥን መያዙን በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሃያ ሁለት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባው ህንፃ ሶስት ቤዝመንቶች፣ አንድ ግራውንድ እና 15 ወለሎች ይኖሩታል።

 

 

በድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ ፌስቡክ https://www.facebook.com/Esdros-Construction-Trade-and-Industry-SC-282021025628947 ይከታተሉ።

አክሲዮን ማህበሩ በነደፈው ስልት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጉዳትን መቀነስ ተችሏል

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታሉ 135 ሚሊዮን ብር መድረሱን የአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አስታወቀ፡፡

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ኮቪድ 19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በድርጅቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት ቀድሞ በመተንተን በተወሰደ እርምጃ ጉዳቱን መቀነስ እንደተቻለ ተገለፀ፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳሲ አቶ ታደሰ አሰፋ እንደገለፁት ቦርዱ ወረርሽኙ በድርጅቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ በመተንትን እና ለእያንዳንዱ ሊከሰት የሚችል ጉዳት ተገቢውን ስልት በማስቀመጥ አስቀድሞ ሰርቷል፡፡

በበርካታ ድርጅቶች ላይ የፋይናንስ ቀውስ ያስከተለው ወረርሽኙ በአክሲዮን ማህበሩ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በተሰራው ስራ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መቀነስ መቻሉን የገለፁት አቶ ታደሰ ሁሉም ሰራተኞች የኢኮኖሚ ችግር ሳይገጥማቸው ደመወዛቸውን እያገኙ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

 

አክሲዮን ማህበሩ ትርፋማነቱን አስቀጥሎ እና ያጋጠሙትን ችግሮች ተቋቁሞ ዛሬ ላይ መድረሱን ያወሱት አቶ ታደሰ፤ ወረርሽኙ በማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ እንቅፋት መደቀኑንም አንስተዋል፡፡ተጨማሪ ት/ቤቶችን ለማስፋፋት እና ከትምህርት ዘርፉ ውጪ ባሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ለመግባት አክሲዮን ማህበሩ በጀመረው እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ለችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና አዳዲስ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ታደሰ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 

 

 

በድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ ፌስቡክ https://www.facebook.com/Esdros-Construction-Trade-and-Industry-SC-282021025628947 ይከታተሉ።

አክሲዮን ማህበሩ 8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውንና 7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ 8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውንና 7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ትናንት በአዲስ አበባ ግሎባል ሆቴል አካሄደ፡፡
በጉባዔው የ8ኛ መደበኛ የጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎችን የማፅደቅ፣ አዳዲስ ባለአክሲዮኖችን የመቀበል፣ የዲሬክተሮች ቦርድ የ2012 በጀት አመት አፈፃፀም ሪፖርት ሰምቶ የማፅደቅ እና የውጪ ኦዲተር ሪፖርት የመስማትና ማፅደቅ ስራ ተከናውኗል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳሲ አቶ ታደሰ አሰፋ የ2012 በጀት አመት ሪፖርትን አቅርበው ውይይት የተደረገበት ሲሆን የበጀት አመቱ የትርፍ ክፍፍል ላይ የመወሰንን ጨምሮ የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት አበል ማፅደቅ እና የ8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለጉባኤ ማፅደቅ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

አክሲዮን ማህበሩ በ2013 ዓ.ም ሊሰራቸው ያቀዳቸው የትኩረት መስኮችን ይፋ ያደረገ ሲሆን በዕለቱ ስብሰባው በ7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎቹ ውስጥ የ7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎችን ያጸደቀ ሲሆን፣ የአክሲዮን ማህበሩን ካፒታል ማሳደግ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

ባለአክሲዮኖችም በቀረቡ ሪፖርቶች ዙሪያ አስተያየት እና ጥያቄዎችን አንስተው ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ወደ ፊት ሊሻሻሉ በሚገባቸውና በትኩረት ሊሰራባቸው በሚገቡ የስራ ዘርፎች ዙሪያ ያላቸውን ምልከታ ገልፀዋል፡፡

 

 

 

 

በድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ ፌስቡክ https://www.facebook.com/Esdros-Construction-Trade-and-Industry-SC-282021025628947 ይከታተሉ።

Abune gorgorios

ለቅድመ መደበኛ ዋና መምህራን ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ

በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ የአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤቶች ለቅድመ መደበኛ ዋና መምህራን ሲሰጥ የቆየው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ማሻሻያ ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ የሰው ሀብት አስተዳደር መምሪያ ስ/አስኪያጅ አቶ ታከለ በኩረ ስልጠናውን አስመልክተው እንደተናገሩት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተማሪዎች በሁሉም የትምህርት አይነቶች ብቁ ሆነው እንዲገኙ የመምህራንን ሁለንተናዊ አቅም መገንባት አስፈላጊና ለነገ የማይባል በመሆኑ ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡

በቀን ለሶስት ሰዓታት ያህል የተሰጠው ይህ ስልጠና በጠቅላላ 30 ሰዐታት የፈጀ ሲሆን መምህራን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ማስቻሉን አቶ ታከለ ገልፀዋል፡፡ አክሲዮን ማህበሩ በቀጣይም መሰል ስልጠናዎችን በማዘጋጀት የመምህራንን ክህሎት የማሳደግና አቅማቸውን በማሻሻል ውጤታማ የማድረግ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚሰራ አቶ ታከለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ከህዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተሰጠው እና የመምህራንን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና እንደተጫወተ በተገለፀው በዚህ ስልጠና ከአምስቱም ትምህርት ቤቶች 30 ዋና የቅድመ መደበኛ ትምህርት መምህራን ተሳትፈዋል፡፡
ስልጠናውን ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ከ’’ቲች ኢትዮጵያ’’ ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ለማወቅ ተችሏል፡፡

Teachers

 

የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/a/ እና የቴሌግራም ቻናል https://t.me/Esdrossc ይከታተሉ፡፡

የስብሰባ ጥሪ : ለኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አንቀጽ 418፤419 ፣ 423 እና 424 በአክሲዮን ማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 9 መሠረት የባለአክሲዮኖች 8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና 7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ እሑድ ታሕሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ግሎባል ሆቴል ይካሔዳል፡፡ ስለሆነም በስብሰባው ላይ በአካል ወይም ሕጋዊ ወኪሎቻችሁ አማካኝነት እንድትገኙ በአክብሮት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

              የ8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች

   1. የ8ኛ መደበኛ የጠቅላላ ጉባዔ አጀንዳዎች ማጽደቅ
   2. አዳዲስ ባለ አክሲዮኖችን መቀበል
   3. የዲሬክተሮች ቦርድ የ2012 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት መስማትና ማጽደቅ
   4. የውጭ ኦዲተር ሪፖርት መስማትና ማጽደቅ
   5. የዲሬክተሮች ቦርድ የ2013 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች መስማትና ማጽደቅ
   6. የ2012 በጀት ዓመት የትርፍ ክፍፍል ላይ መወሰን
   7. የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት አበል ማጽደቅ
   8. የ8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባኤ ማጽደቅ

               የ7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች

   1. የ7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች ማጽደቅ
   2. የአክሲዮን ማኅበሩን ካፒታል ማሳደግ
   3. የ7ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ማጽደቅ

   

ማሳሰቢያ

 1. በአካል ለሚገኙ ባለአክሲዮኖች የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ፣ ፖስፖርት ወይም መንጃ ፈቃድ እንዲይዙ፡፡
 2. ተወካዮች ሕጋዊ የውክልና ማስረጃ ዋናውን እና ፎቶ ኮፒውን እንዲሁም የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ወይም የመንጃ ፈቃድ ይዘው እንዲቀርቡ፡፡
 3. በኮቪድ 19 ምክንያት አዳራሹ መያዝ የሚችለው የተሳታፊዎች ብዛት ከመደበኛው ሩቡን ስለሆነ ባለአክሲዮኖች በውስን ሕጋዊ ወኪሎቻችሁ በኩል መሳተፍ እንድትችሉ ተገቢውን ውክልና እንድትሰጡና በጉባኤው ላይ የሚገኙ ሁሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንድታደርጉ በአክብሮት መልእክታችን እናስተላልፋለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ በስልክ

0930-363-779

0930-363-949

0118-688-450/51

በመጠቀም መደወል የምትችሉ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን፡፡

የዲሬክተሮች ቦርድ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር

 

Abune gorgorios

የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራን ጀመሩ

በኤስድሮስ ኮንስትራክሽን፣ ንግድና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራ መጀመራቸው ተገለፀ፡፡

ትምህርት ቤቶቹ በአለም አቀፍ ብሎም በሀገር ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የገፅ ለገፅ ትምህርት መንግስት ባወጣው መመሪያ መሰረት በፈረቃ እያከናወኑ ሲሆን ይህንንም ለማገዝ ያመች ዘንድ የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራን ዛሬ ጀምረዋል፡፡

የአክሲዮን ማህበሩ የትምህርት ዘርፍ ተወካይ አቶ ዘሪሁን ክብረት እንደገለፁት ተማሪዎች በቤታቸው በሚሆኑባቸው የትምህርት ቀናት ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ታስቦ የተዘጋጀው የኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራ ከአፀደ ህፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በተመጠነ መንገድ ይሰጣል፡፡

ያለምንም የጊዜና የቦታ ገደብ የትምህርት ይዘቶችን ጥራትና አግባብነት በማሻሻል በጥራትና በብቃት ትምህርትን ለማድረስ ያስችላል የተባለለት ኢ-ለርኒንግ፤ ምዘናን ወጥነት ባለው  መንገድ ተግባራዊ ከማድረጉም በላይ የክፍል ውስጥ መማር ማስተማርን  እንደሚደግፍ አቶ ዘሪሁን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ከትምህርት ቤቶቹ የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ መዘጋጀቱን ያብራሩት አቶ ዘሪሁን ትምህርቱን ለመስጠት መሰረታዊ ግብዓት የሚሆኑ ማዕከላዊ ማስታወሻዎች፣ መለማመጃ ጥያቄዎችና ሙከራዎች፣ የትምህርት ገለፃ ቪዲዮዎች፣ ለዲጂታል ቤተመፅሀፍት የሚያገለግሉ መፅሀፍት እና ሌሎችም ተዘጋጅተው ወደመጀመሪያ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል፡፡

ወላጆች ትምህርቱን በተገቢው መንገድ ለተማሪዎች ለማድረስ አቅም በፈቀደ መጠን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን እንዲያዘጋጁ፣ ከት/ቤቶቹ የሚወጡ መመሪያዎችን መነሻ በማድረግ የአጠቃቀም እውቀት እንዲይዙና ተማሪዎችም ለትምህርቱ የሚውሉ መገልገያዎችን ላልተፈለገ አላማ እንዳይጠቀሙ ክትትል እንዲያደርጉ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

ትምህርቱን ከዛሬ ህዳር 29 ቀን ጀምሮ elearning.esdros.com ላይ በመግባት ማግኘት እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡

ኢ-ለርኒንግ የመማር ማስተማር ስራ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማለትም ኮምፒዩተር፣ ስማርት ስልኮች፣ ታብሌቶችና አይፎኖችን ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በማገናኘት ለተማሪዎች ትምህርትን ማድረስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

E-Learning

የአክሲዮን ማህበራችንን ድህረ ገፅ https://esdros.com/e/ እና የቴሌግራም ቻናል https://t.me/Esdrossc ይከታተሉ፡፡

የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የገፅ ለገፅ ማስተማር ስራቸውን ጀመሩ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የገፅ ለገፅ ማስተማር ስራቸውን ትናንት በይፋ ጀምረዋል፡፡
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለወራት ተቋርጦ የነበረው የገፅ ለገፅ ትምህርት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ከህዳር 21 ቀን ጀምሮ መሰጠት እንዲጀምር የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርቱን መስጠት ጀምረዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ትምህርቱን የጀመሩ ሲሆን የትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰብ እና ተማሪዎች ወረርሽኙን ለመከላከል የተቀመጡ ፕሮቶኮሎችን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡

የአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የሲኤምሲ ቅርንጫፍ ርዕሰ መምህር አቶ እስክንድር ገመቹ በትምህርት መክፈቻ ስነስርዐቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ዘመቻ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀው በትምህርት ቤቱ የተቀመጡ ህጎችን በማክበር ጤናቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የተማሪዎችን ተጋላጭነት ለመከላከል ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የተቀመጡ የወረርሽኝ መከላከያ ፕሮቶኮሎችን ተግባራዊ እያደረገ ስለመሆኑ የገለፁት አቶ እስክንድር፤ ትምህርቱ ከስጋት ነፃ በሆነ መንገድ እንዲሰጥ ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች ከጥቅምት 16 ቀን ጀምሮ ለስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ትምህርት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ትናንት እና ዛሬ ደግሞ ሞዴል ፈተናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ፤ የፊታችን ህዳር 24 እና 25 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ትምህርት ቢሮ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ክልል አቀፍ ፈተናቸውን የሚወስዱ ይሆናል፡፡

በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ስራው የተሳለጠና የተቀመጠለትን ግብ ይመታ ዘንድ በሁሉም ቅርንጫፎች የሚሰሩ መምህራን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

አክሲዮን ማህበሩ የታክስ ህግ ተገዥነት ተሸላሚ ሆነ

ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ በ2012 በጀት አመት ለታክስ ህግ ተገዥነት ባስመዘገበው ውጤት በገቢዎች ሚኒስቴር ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የመካከለኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ህግ ተገዥነትን በማክበርና በመተግበር የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የንግድ ተቋማት የኢፌዲሪ ገቢዎች ሚኒስቴር ህዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም ባዘጋጀው የሽልማትና እውቅና ፕሮግራም ላይ ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ለታክስ ህጉ ተገዥ በመሆን ላስመዘገበው ውጤት የዋንጫና ምስክር ወረቀት ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

በካፒታል ሆቴል በተካሄደው በዚህ ስነስርዓት ላይ አክሲዮን ማህበሩ በቀጣይም ለህግ ተገዥነትን የንግድ እንቅስቃሴው መርህ አድርጎ ግብሩን በወቅቱና በአግባቡ እንደሚከፍል በአዘጋጆቹ እምነት እንደተጣለበት የተገለፀ ሲሆን ሽልማቱን የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ተቀብለዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ ትውልድን በማነፅ ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋን በማፍራት ላይ የሚገኘው ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ ሁሉንም የግብር አይነቶች በታክስ ህጉ መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እየከፈለ ሲሆን ይህም ማህበሩ ከተቋቋመለት አላማ አንፃር የሚጠበቅ እና በትኩረት የሚሰራበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አክሲዮን ማህበሩ በየአመቱ ሂሳቡን ኦዲት በማስደረግ ለገቢዎች እያሳወቀ ሲሆን ታክሱን በተገቢው ጊዜና መጠን እየከፈለ እንደሚገኝ በዚህም ለሽልማት መብቃቱን አቶ ተስፋየ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ሽልማቱ ኤስድሮስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ አ.ማ በተሰማራባቸውና ወደፊትም ሊሰራቸው በእንቅስቃሴ ላይ በሚገኝባቸው የስራ ዘርፎች ግብሩን በታማኝነት በመክፈልና ለታክስ ህጉ ተገዥ በመሆን የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስቻለው መሆኑን አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

ውድ የተማሪዎቻችን ወላጆች/አሳዳጊዎች

በማስቀደም እንኳን ለ2013 ዓ.ም ትምህር ዘመን በሰላም አደረሳችሁ እንላለን!

እንደሚታወቀው ትምህር ቤታችን በኮቪድ 19 አለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት የገጽ ለገጽ ትምህርት ከተዘጋበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በተላይም የቴሌግራም ቻናሎችን በመክፈት በተቻለ አቅም ሁሉም ተማሪዎች ከትምህር ውጪ እንዳይሆኑና የተማሩትን እንዳይዘነጉ እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በፈረቃ ትምህርቱ እንዲቀጥል በተወሰነው መሰረት ዝግጅቶቻችንን አጠናቀን ተማሪዎቻችን ለመቀበል እየተጠባበቅን ቢሆንም የአዲስ አበባ ትምህር ቢሮ የመክፈቻው ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን አሳውቋል፡፡ በመሆኑም መማር ማስተማሩን ይበልጥ ሙሉ ለማድረግና የሚባክኑትን ጊዜያት ለማካካስ በማሰብ በተለይም ተማሪዎች ቤት በሚውሉበት ቀናት ከትምህር ተግባራት ውጪ እንዳይሆኑ ለጊዜው የቴሌግራም ቻናሎችን በመጠቀም ትምህርቱ እንደሚቀጥል እንገልጻለን፡፡ ትምህር ቤታችን በቀጠይ በቨርቹዋል የማስተማር መንገድ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ለመማር መስተማሩ ምቹ የሆነ ቴክኖሎጂ Learning Management System (LMS) ለማስጀመር ሙሉ ዝግጅቱን በመጠናቀቁና ወደትግበራ መገባት ላይ በመሆኑ አማረጮቹን ለመጠቀም እንድትዘጋጁ እናሳውቃለን፡፡